Joshua 22

ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ርስት ያገኙ ነገዶች ወደ ቤታቸው ተመለሱ

1በዚህ ጊዜ ኢያሱ የሮቤልንና የጋድን ነገዶች፣ እንዲሁም የምናሴን ነገድ እኩሌታ ጠርቶ 2እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ ጠብቃችኋል፤ እኔም ያዘዝኋችሁን በሙሉ ፈጽማችኋል፤ 3ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ተልእኮ በሚገባ ተወጥታችኋል። 4አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ወንድሞቻችሁን አሳርፏቸዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ ርስት አድርጎ በሰጣችሁ ምድር ወዳለው ቤታችሁ ተመለሱ። 5የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን እንድትወዱ፣ በመንገዱ ሁሉ እንድትሄዱ፣ ትእዛዙን እንድትፈጽሙ፣ እርሱንም አጥብቃችሁ እንድትይዙት እንዲሁም በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁ እንድታገለግሉት የሰጣችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ነቅታችሁ ጠብቁ።”

6ከዚያም ኢያሱ መርቆ አሰናበታቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 7ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በባሳን ምድር ርስት ሰጥቷቸው ነበር፤ ለቀረው እኩሌታ ደግሞ ኢያሱ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። ኢያሱ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ባሰናበታቸው ጊዜ መረቃቸው፤ 8እንዲህም አላቸው፤ “ብዙ ሀብት ይዛችሁ ማለትም አያሌ የከብት መንጋ፣ ብርና ወርቅ፣ ናስና ብረት እንዲሁም ቍጥሩ እጅግ የበዛ ልብስ ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ ከጠላት የተገኘውንም ይህን ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉት” አላቸው።

9ስለዚህ የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ እስራኤላውያንን ከነዓን ውስጥ ባለችው በሴሎ ትተው፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝ በሙሴ አማካይነት ወደ ተቀበሏት ርስታቸው፣ ወደ ገለዓድ ምድር ተመለሱ።

10የሮቤልና የጋድ እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነዓን ምድር ወዳለችው፣ ዮርዳኖስ አጠገብ ወደምትገኘው ገሊሎት ወደ ተባለች ስፍራ ሲደርሱ በወንዙ አጠገብ ግዙፍ መሠዊያ ሠሩ። 11የእስራኤላውያን ይዞታ በሆነችው በከነዓናውያን ምድር ወሰን በገሊሎት ላይ መሠዊያ መሥራታቸውን ሌሎቹ እስራኤላውያን በሰሙ ጊዜ፣ 12በእነርሱ ላይ ለመዝመት የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ።

13ስለዚህም እስራኤላውያን የካህኑ የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን በገለዓድ ምድር ወደሚኖሩት ወደ ሮቤልና ወደ ጋድ እንዲሁም ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ላኩ፤ 14ከእርሱም ጋር እያንዳንዱን የእስራኤልን ነገድ የሚወክሉ ዐሥር አለቆች አብረው ላኩ፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው ከእስራኤላውያን ጐሣዎች የተውጣጡ የየቤተ ሰቡ አለቆች ነበሩ።

15እነርሱም በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያንና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ሄደው እንዲህ አሏቸው፤ 16“መላው የእግዚአብሔር ጉባኤ እንዲህ ይላል፤ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ክሕደት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን ከመከተልስ እንዴት ወደ ኋላ ትላላችሁ? እንዴትስ ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችሁ ለራሳችሁ መሠዊያ ትሠራላችሁ? 17በፌጎር የተሠራው ኀጢአት አይበቃንምን? ምንም እንኳ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ መቅሠፍት ቢወርድም፣ እስከ ዛሬዪቱ ዕለት ድረስ ራሳችንን ከዚያች ኀጢአት አላነጻንም። 18እናንተ፣ አሁንም እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ትላላችሁን?

“ ‘ዛሬ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ፣ እርሱ ደግሞ ነገ በመላው እስራኤል ጉባኤ ላይ ይቈጣል።
19የወረሳችኋት ምድር ረክሳ እንደ ሆነ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደ ተተከለበት ወደ እግዚአብሔር ምድር መጥታችሁ ከእኛ ጋር ርስት ተካፈሉ፤ ነገር ግን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ በስተቀር ሌላ መሠዊያ ሠርታችሁ በእግዚአብሔርም ሆነ በእኛ ላይ አታምፁ። 20የዛራ ልጅ አካን፣ ዕርም የሆነውን ነገር በመውሰድ ኀጢአት ስለ ሠራ፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ላይ ቍጣ አልመጣምን? በሠራው ኀጢአት የሞተውም
የዕብራይስጡ ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው።
እርሱ ብቻ አልነበረም።’ ”

21ከዚያም የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል ጐሣ መሪዎች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ 22“ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር! ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር! እርሱ ያውቃል! እስራኤልም ይህን ይወቅ! ይህ የተደረገው በማመፅ ወይም ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ከሆነ፣ ዛሬ አትማሩን! 23መሠዊያውን የሠራነው እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ለማለት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ልናሳርግበት ወይም የኅብረት መሥዋዕት
በዚህና በቍጥር 27 ላይ በትውፊት የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል።
ልናቀርብበት አስበን ከሆነ፣ ራሱ እግዚአብሔር ይበቀለን።

24“እኛማ ይህን ያደረግነው፣ ወደ ፊት ዘሮቻችሁ ለዘሮቻችን እንዲህ እንዳይሏቸው ፈርተን ነው፤ ‘ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን ግንኙነት አላችሁ? 25እናንት የሮቤልና የጋድ ልጆች፤ እግዚአብሔር ዮርዳኖስን በመካከላችን መለያ ድንበር ስላደረገው፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም።’ ስለዚህ ዘሮቻችሁ፣ የእኛ ዘር እግዚአብሔርን እንዳይፈራ ሊያደርጉ ይችላሉ።

26“እኛም ‘እንነሣና መሠዊያ እንሥራ፤ የምንሠራው መሠዊያ ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ አይውልም’ ያልነው ለዚህ ነው። 27በሌላም በኩል የሚቃጠል መሥዋዕታችንን፣ ሌላውን ቍርባናችንንና የኅብረት መሥዋዕታችንን ይዘን በተቀደሰው ስፍራ እግዚአብሔርን እንደምናመልክ መሠዊያው በእኛና በእናንተ እንዲሁም በሚቀጥሉት ትውልዶች መካከል ምስክር ይሆናል። ስለዚህ ወደ ፊት ዘሮቻችሁ ዘሮቻችንን፣ ‘ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም’ ሊሏቸው አይችሉም።

28“እኛም፣ ‘ወደ ፊት እኛንም ሆነ ዘሮቻችንን እንዲህ የሚሉ ከሆነ፣ “እነሆ፤ አባቶቻችን የሠሩትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ ተመልከቱ፤ ይህ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር እንዲሆን እንጂ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ አይደለም” ብለን እንመልሳለን’ አልን።

29“በማደሪያው ድንኳን ፊት ካለው ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለእህል ቍርባን እንዲሁም ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ የሚሆን መሠዊያ በመሥራት ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ እናምፅን? እርሱን ማምለካችንንም እንተውን? ይህ ከእኛ ይራቅ!”

30ካህኑ ፊንሐስና የእስራኤላውያን የጐሣ መሪዎች የነበሩት የማኅበረ ሰቡ አለቆች የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ወገኖች ያሉትን በሰሙ ጊዜ ተደሰቱ። 31የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም፣ የሮቤልን የጋድንና የምናሴን ወገኖች “በዚህ ነገር እግዚአብሔርን አልበደላችሁምና፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ዛሬ ዐውቀናል፤ እነሆ እስራኤላውያንን ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል” አላቸው።

32ከዚያም የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና መሪዎቹ፣ ከሮቤልና ከጋድ ወገኖች ጋር በገለዓድ ምድር ከተነጋገሩ በኋላ፣ ወደ ከነዓን ተመልሰው፣ ሁኔታውን ለእስራኤላውያን ነገሩ። 33እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ከዚያም የሮቤልና የጋድ ወገኖች የሚኖሩበትን አገር በጦርነት ለማጥፋት የመሄድን ነገር አላነሡም።

34የሮቤልና የጋድ ወገኖችም፣ እግዚአብሔር አምላክ ለመሆኑ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው፤ በማለት መሠዊያውን “ምስክር” ብለው ጠሩት።

Copyright information for AmhNASV